http://www.abbaabiyya.com

በአንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ተባለ

464

አሁን እየታየ ያለው የዝናብ መጠን የሚቀጥል በመሆኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ተባለ።

የብሄራዊ ሚቲዮሮሎጅ ኤጀንሲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የዘንድሮው የክረምት ወቅት የዝናብ ስርጭቱ እና መጠኑ የተስፋፋ ሆኖ መታየቱን አስታውቋል።

ያለፉት ሁለት የክረምት ወራቶች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኙበት እና አንዳንድ ቦታዎች ላይም የጎርፍ አደጋ የታየበት መሆኑን አመላክቷል።

ለክረምቱ የዝናብ ስርጭት እና መጠን መጨመርም በበልግ ወራት የነበረው የዝናብ መጠን እና የክረምት ጊዜው ቀድሞ መግባት አስተዋፅኦ ማድረጉንም ኤጀንሲው ገልጿል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምስራቅ እንዲሁም መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የክረምቱ ዝናብ መጠን ከፍ ማለትና ከተለመደው በላይ መሆን በተለያዩ አካባቢዎች ጎርፍ እንዲከሰት አድርጓልም ነው ያለው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ አሁን ያለው የዝናብ ስርጭት እና መጠን በቀጣዮቹ ሳምንታት ማለትም እስከ መስከረም ወር ማጠናቀቂያ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

Comments are closed.